ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ዐርጎ በእግዚአብሔር ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በምድር ላይ የእርሱን ስፍራ የያዙት አማኞች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ይመለከታል፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን ራስ እንደመሆኑም በምድር ላይ በእርሱ ስም በየስፍራው የተሰበሰቡትን አብያተ ክርስቲያናት ያስተዳድራል፡፡ ይህም ማለት በመካከላቸው እየተሠራ ባለው ነገር ላይ ይበይናል፤ የሚነቀፈውን ይነቅፋል፤ የሚበረታታውን ያበረታታል፣ የሚፈረድበትን ይፈርድበታል፡፡ ይህንንም እውነታ በእስያ ለነበሩት ለሰባቱ አብያተክርስቲያናት ባስተላለፋቸው ሰባት መልእክታት ውስጥ በግልጽ እንገነዘባለን፡፡
እነዚህ ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት የተጻፉ መልእክታት የሚገኙት በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ 2 እና ምዕራፍ 3 ውስጥ ሲሆን መልእክታቱን ለእያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ያስተላለፈው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በራእ.1፡1-2 ላይ «... ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ» የሚለውንና በቊ.10 «በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፤ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፤ እንዲሁም የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ፣ ወደ ጴርጋሞንና ወደትያጥሮንም፣ ወደ ሰርዴስም፣ ወደ ፊልድልፍያም፣ ወደ ሎዶቅያም፣ በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ» የሚለውን ስናነብ በዮሐንስ እጅ መልእክቱን ያስጻፈውና የላከው ራሱ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን በግልጽ እንረዳለን፡፡ በቊ.5 ላይ ደግሞ «ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት» የሚል ቃል እናነባለን፤ ይህ የሚያመለክተው ባለራእዩ ሐዋርያው ዮሐንስ መልእክታቱንም ሆነ ጠቅላላ ራእዩን ከጌታ ተቀብሎ ለሰባቱ አብያተክርስቲያናት በጽሑፍ ማስተላለፉን ነው፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «እስያ» ተብሎ የተጠቀሰው አገር አሁን የሚታወቀውን ታላቁን ምሥራቃዊ ክፍለ ዓለም /አህጉር/ የሚያመለክት አይደለም፤ ነገር ግን በዚሁ በምሥራቃዊ ክፍለ ዓለም ምዕራባዊ ዳርቻ የነበረ አንድ አነስተኛ አገር ነው፡፡ በሐዋ.ሥ.2፡9-10 ስንመለከት «... በቀጰዶቅያም፣ በጳንጦስም፣ በእስያም፣ በፍርግያም፣ በጵንፍልያም ....» የሚል እናነባለን፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ «እስያ» በምሥራቃዊው ክፍለ ዓለም በምዕራባዊ ዳርቻ ከሚገኙ የተለያዩ አነስተኛ ጎረቤት አገሮች ጋር ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ በዚሁም ዓይነት በሐ.ሥ.16፡6 እና በ1ጴጥ.1፡1 ላይ ስንመለከት እስያ በዚያው አካባቢ ይገኙ ከነበሩት ከፍርግያ፣ ከገላትያ፣ ከጳንጦስ፣ ከቀጰዶቅያና ከቢታንያ አገሮች ጋር እንደ አንድ አገር ተገልጾ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም በእስያ የሚገኙት ሰባቱ አብያተክርስቲያናት በሰባት የተለያዩ ከተሞች የነበሩ ሲሆን እነዚህም ከተሞች በራእ.1፡10 ላይ ከላይ እንደተመለከትናቸው ኤፌሶን፣ ሰምርኔስ፣ ጴርጋሞን፣ ትያጥሮን፣ ሰርዴስ፣ ፊልድልፍያ፣ እና ሎዶቅያ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ከተሞች በጊዜው የእስያ ዋና ከተማ ኤፌሶን ነበረች፡፡ ወደ እስያ አገር ወንጌል የደረሰው በሐዋርያው በጳውሎስ አማካኝነት እንደሆነ ከሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 19 እንረዳለን፡፡ ይህ ሐዋርያ በዋና ከተማዋ በኤፌሶን በአይሁድ ምኲራብና ጢራኖስ በሚሉት ት/ቤት ባገለገለው የወንጌል አገልግሎት በእስያ ሁሉ ወንጌል ሊዳረስ ችሏል፡፡ «በእስያ የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል ሆነ፡፡» ተብሎ የተጻፈው ቃል ይህንኑ ያስረዳል /ሐ.ሥ.19፡10/፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱ ወደ መቄዶንያ በሄደ ጊዜ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ተቀምጦ «አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ» ያዝዛቸው ዘንድ አድርጎ ነበር /1ጢሞ.1፡3-4/፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስም በሕይወቱ ፍጻሜ ገደማ በእስያ ያገለግል እንደነበረ የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ ለእስያ አብያተክርስቲያናት የተጻፈ በመሆኑ ልንገነዘብ እንችላለን፡፡ ጌታ ለእነዚህ አብያተክርስቲያናት መልእክታቱን ዮሐንስ እንዲጽፍላቸው ያዘዘው እርሱ ቀደም ሲል አብሮአቸው የኖረ ስለሆነ ነው ብለን ለማሰብ እንችላለን፤ እንደዚሁም ዮሐንስ ራሱ «እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ፣ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል» ብሎ የጻፈላቸው ቃል እርሱ ቀደም ሲል ከእነርሱ ጋር አብሮ የነበረና በአካል የሚያውቃቸው እንደሆነ አመላካች ነው /ራእ.1፡9/፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ራእዩን ያየውና ለሰባቱ አብያተክርስቲያናት የጻፈላቸው መልእክታቱንም ከጌታ የተቀበለው ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ፍጥሞ ከእስያ በስተደቡብ ምዕራብ በኩል ካለው ዳርቻ 55 ኪ.ሜ. ያህል ርቃ በኤጂያን ባሕር ውስጥ የምትገኝ አነስተኛ ደሴት ናት፤ ርዝመቷ 12 ኪ.ሜ. ወርዷ 7 ኪ.ሜ. የሆነች ሞቃታማና አለታማ ደሴት ናት፡፡ በነዮሐንስ ዘመን በሮማ ግዛት ውስጥ ዓመፀኞች የሚባሉ ሰዎች የሚታሰሩባት የቅጣት ቦታ ነበረች፡፡ ዮሐንስ ምንም ጥፋት ሳይገኝበት ራሱ እንደገለጠው ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለኢየሱስ ምስክር በዚህች ደሴት ታስሮ ሳለ ዙሪያውን ከማንም እንዳይገናኝ ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጌታ ቀን በመንፈስ በሆነ ጊዜ ሰማዩ ተከፍቶለት ነበር፡፡ በዚያ ቀንም የጌታን ድምፅ ሲሰማ ጌታንም በሚያስፈራው ክብሩ ሆኖ በሰባት የወርቅ መቅረዞች መካከል ሲያየው እንደነበር እናነባለን፡፡ ከዚያ በኋላም ጌታ ኢየሱስ በቅድሚያ ዮሐንስ ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት የሚጽፍላቸውን መልእክታት ሲነግረው እንመለከታለን፡፡
ለሰባቱ የእስያ አብያተክርስቲያናት የተላለፉት እነዚህ መልእክታት በይዘታቸው በወቅቱ በእስያ ውስጥ በነበሩት ሰባት ከተሞች የሚገኙት ሰባት አብያተክርስቲያናት የነበራቸውን መንፈሳዊ ሁኔታ የሚመለከቱ ናቸው፤ ከዚህ አንጻር በዘመናችን በየስፍራው ያሉ ጉባኤዎች /አብያተክርስቲያናት/ ላሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ማበረታቻም ሆነ ማረሚያ የሚሆን መልእክት ሊያገኙባቸው ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ እስከ አማኞች መነጠቅ ድረስ ባለው በጠቅላላው የቤተክርስቲያን ዘመን /የጸጋው ዘመን/ በየክፍለ ዘመናቱ ሊሆን የነበረውንና ሊሆን ያለውን የቤተክርስቲያንን ሕይወት በትንቢት የሚናገሩ መልእክታት ናቸው፡፡ ሰባት የእግዚአብሔር ፍጹም ወይም ሙሉ ቊጥር መሆኑ ይታወቃል፤ ስለሆነም መልእክታቱ በሰባት ቊጥር ተወስነው ለሰባቱ አብያተክርስቲያናት መተላለፋቸው በእግዚአብሔር የተወሰነው የቤተክርስቲያን ዘመን ፍጻሜ እስኪመጣ ድረስ ያለውን ሙሉውን ጊዜ ሊያመለክተን ይችላል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰባቱ መልእክታት ትንቢታዊ ገጽታ እንዳላቸው ሁለት ዋና ዋና ማስረጃዎች አሉ፤ እነርሱም እንደሚከተለው ይተነተናሉ፡፡
ከእነዚህ ክፍሎች መካከል «አሁን ያለው» የተባለው ክፍል በዚያ በዮሐንስ ዘመን ያለው ማለት ሳይሆን ባጠቃላይ አሁን በቤተክርስቲያን ዘመን ያለው ለማለት ነው፤ ምክንያቱም በራእ.4፡1 ጀምሮ «ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገው» የተባለው ትንቢት ሲጀምር እናያለን፤ ከምዕ.4 በኋላ የተገለጠው ደግሞ በዚህ በቤተክርስቲያን ዘመን ያልተፈጸመና የማይፈጸም ሲሆን ቤተክርስቲያን ከተነጠቀች በኋላ በሚመጣው የመከራው ዘመንና ከዚያ በኋላ የሚሆኑ ነገሮችን የያዘ ክፍል ነው፤ «ቤተክርስቲያን» የሚለውንም ቃል ከዚያ በኋላ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እስከ ምዕ.21 ድረስ አናገኘውም፤ ስለዚህ «አሁን ያለው» ሲል የቤተክርስቲያን ዘመን አብቅቶ ያ የመከራ ጊዜ እስኪጀምር ድረስ መሆኑ ግልጽ ነው፤ ከዚህ አንጻር ስንመለከት ለሰባቱ የእስያ አብያተ ክርስቲያናት የተጻፉት ሰባቱ መልእክታት ምንም እንኳ ራእዩ በታየበት በዚያው ዘመን ለነበሩ ሰባት ጉባኤዎች የተላለፉ መልእክታት ቢሆኑም በትንቢታዊ ገጽታቸው ጌታ ለቅዱሳኑ እስከሚመጣበት እስከ መነጠቅ ድረስ በምድር ላይ ያለችዋ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ያለፈችበት አጠቃላይ ሁኔታን ያመለክታሉ፡፡ እዚህ ላይ በምድር ላይ ያለችዋ ቤተክርስቲያን ስንል በስመ ክርስትና የሚጠራውን ዓለም በጠቅላላ ማለታችን መሆኑን አንባቢው ከግንዛቤ ውስጥ ሊያስገባው ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የተጻፉትን መልእክታት እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ስናጠና በመጀመሪያ በየስፍራው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለምንሰበሰብባቸው ጉባኤዎች /አጥቢያ ቤተክርስቲያናት/ የሚሆን ተግባራዊ መልእክትን የምናገኝ ሲሆን ከዚህም በላይ ደግሞ በጠቅላላ በክርስትናው ዓለም ባለፉት ዘመናትም ሆነ በዘመናችን እንዲሁም በሚመጡት ጊዜያት የሆነውንና የሚሆነውን እናይበታለን፡፡
ሰባቱ መልእክታት ባላቸው አቀራረብ የሚመሳሰሉባቸው መንገዶች አሉ፡፡ በዚህም ተመሳሳይ አቀራረባቸው ተመሥርተን ሰባቱንም መልእክታት በአራት ልንከፍላቸው እንችላለን፤ ይኸውም፡-
«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» የሚለው ምክር በሰባቱም መልእክታት
ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሦስት መልእክታት ውስጥ ድል ለነሳው ከተሰጠው ተስፋ በፊት፣ በቀጣዮቹ 4 መልእክታት ውስጥ ደግሞ ድል ለነሳው ከተሰጠው ተስፋ በኋላ የተነገረ ቃል ነው፤ ይህም ቃል ለአንድ ቤተክርስቲያን የተነገረው ምክር ለአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተላለፈ መልእክት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን የሚገኘው አማኝ እርሱ ለሚገኝባት ቤተክርስቲያን የተላለፈውን መልእክት ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም የተላለፉትን መልእክታትም
ሊመለከታቸውና ሊታዘዝላቸው ይገባል፤ እኛም «መልእክቱ በዚህ ዘመን ለምንገኝ ለእኛም ነው» እያልን ለእያንዳንዷ ቤተክርስቲያን የተጻፉትን መልእክታት በዝርዝር ማጥናታችንን እንቀጥላለን፡፡