"ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም"
በርእሱ የተመለከተውን መሪ ቃል ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፤ የጽሑፉም መነሻ የቆሮንቶስ አማኞች እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው በተለያየ መሠረት ላይ የሚቆሙበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው፤ ሐዋርያው ከመጀመሪያው ምዕራፍ ጀምሮ ሲናገር «ወንድሞች ሆይ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለእናንተ የቀሎዔ ቤተሰዎች አስታውቀውኛልና» ይላል /1ቆሮ.1፡11/፡፡ በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ሰዎች መጀመሪያ የጌታ ኢየሱስን ወንጌል የሰበከላቸውና ወደ ጌታ ለመምጣታቸው እንደመሣሪያ የሆነው ጳውሎስ ነበር /ሐ.ሥ.18፡1/፡፡ ጳውሎስ ከቆሮንቶስ ወጥቶ ከሄደ በኋላ ሌሎች አገልጋዮችም ወደ ቆሮንቶስ መጥተው በዚያ የተሰበሰበችውን ጉባኤ አገልግለዋል፡፡ ከእነዚህም አገልጋዮች መካከልም አጵሎስ፣ ኬፋ ማለትም ጴጥሮስ ይገኙባቸዋል፡፡ የቆሮንቶስም ሰዎች በመካከላቸው የነበሩትን ክርክሮች በፍቅር መፍታትና አብሮ መኖር ሳይችሉ ሲቀሩ እንደመፍትሔ የተከተሉት መንገድ ባገለገሉአቸው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ስም ቡድን መፍጠር ነበር፡፡ ስለሆነም ከማህበሩ የተወሰነው የጳውሎስ ነኝ ሲል ሌላው ወገን ደግሞ ይሻለኛል ብሎ በማሰብ ራሱን የአጵሎስ ነኝ ማለትን መረጠ፤ የተቀሩት ደግሞ ምናልባትም ወደ ጴጥሮስ በመሳባቸው ሊሆን ይችላል በጴጥሮስ ስም ራሳቸውን ሲያስቀምጡ ሌሎች ደግሞ በዚያው የቡድን መንፈስ ክርስቶስን ወደነጳውሎስ፣ አጵሎስና ኬፋ ደረጃ ዝቅ አድርገው እኛ የክርስቶስ ነን አሉ፤ ይህንንም ሐዋርያው ሲገልጥ «ይህንም እላለሁ፤ እያንዳንዳችሁ እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፣ እኔስ የክርስቶስ ነኝ ትላላችሁ፡፡ ክርስቶስ ተከፍሏልን? ጳውሎስስ ስለእናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?» ብሏቸዋል /1ቆሮ.1፡12-13/፡፡ እንግዲህ ይህ በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የተፈጠረው መለያየት እጅግ አደገኛና የክርስቶስን ምስክርነት የሚያበላሽ ሆኖ በመገኘቱ የእግዚአብሔር መንፈስ በባሪያው በጳውሎስ በኩል ምላሽ ሲሰጥበት ይታያል፡፡
በአንዱ በክርስቶስ እንደዳኑ የተመሰከረላቸው ሰዎች ክርስቶስን ትተው ስለእርሱ በመሰከሩላቸው አገልጋዮች ስም ሲከፋፈሉ ይህ የጌታን ክብር በእጅጉ የሚያቃልል ነው፡፡ ክርስቶስ አስቀድሞም አልተከፈለም፤ በባሕርዩም መከፈል የለበትም፤ በቃሉም መለያየት የለበትም፤ አካሉ የምትሆን ቤተክርስቲያኑም እንዳትከፈል በመፈለጉ «አንተ እንደላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ» በማለት ስለአካሉ አንድነት ጸሎት አቅርቦ ነበር /ዮሐ.17፡20-23/፡፡ ሆኖም ግን እስራኤል ከግብፅ ተጠርቶ ኋላ ግን ራሱ ከባርነት ነጻ ካወጣው አምላኩ በማፈግፈጉ ከገባባት ርስት ተነቅሎና ወደባቢሎን ተወስዶ ለግዞት እንደተዳረገ ሁሉ አሕዛብም በእግዚአብሔር ርኅራኄ ከተጠሩበት የመንፈስ ኑሮ ወደ ሥጋዊነት ፈቀቅ ብለው ከጸጋው እየወደቁ ስናይ ሰው ምንኛ አሳዛኝ ፍጡር ነው ብለን ለማሰብ እንገደዳለን፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ በቆሮንቶስ አንዲቱ የክርስቶስ አካል ለአራት ትከፈል ነበር፡፡ በሌላ አባባል ይህንን የጠላት ሥራ እግዚአብሔር ባያከሽፈው ኖሮ አንዲቱ ጉባኤ ለአራት ተከፍላ ምናልባትም ከፊሎቹ ኬፋን መሠረት ያደረገ «የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን»፣ ሌሎች ደግሞ አጵሎስን መሠረት በማድረግ «የቅዱስ አጵሎስ ቤተክርስቲያን» ሦስተኛው ቡድን ደግሞ ጳውሎስን መሠረት ያደረገ «የቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን»፣ የተቀሩት ደግሞ መለያየቱን መሠረት አድርገው «የክርስቶስ ቤተክርስቲያን» ወይም ተመሳሳይ ቡድናዊ/ሴክታሪያን/ ቤተእምነት ሊመሠርቱ ይችሉ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ይህም ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተስፋፋ አንዲቱን የክርስቶስን አካል በእጅጉ በከፋፈለ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረጉ አግባብ ካለመሆኑም የተነሣ ፈጽሞ መንፈሳዊነት የጎደለውና ያዳናቸውን ጌታ አለማወቅ በመሆኑ ሐዋርያው «ጳውሎስስ ስለእናንተ ተሰቀለን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠመቃችሁን?» ሲላቸው እንመለከታለን፡፡ እዚህ ላይ በጥቂቱ ቆም ብለን ብናስብ የእነዚህ ሰዎች መሠረታዊ ችግር ያለው በመካከላቸው የተከሰተውን ልዩ ልዩ ክርክር በፍቅርና በትህትና በመፍታት አብረው መኖር ሳይችሉ ሲቀሩ አገልጋዮችን እንደእምነት መሠረት አድርጎ በእነርሱ ስም ለመሰባሰብ መፈለጋቸው ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጳውሎስም ምንም እንኳን የተመረጠ ዕቃ /ሐ.ሥ.9፡15/ ቢባልም የእምነት መሠረት አይደለም፤ እንዲሁም ጴጥሮስ ብፁዕ ቢባልም /ማቴ.16፡17/ ጴጥሮስን ብፁዕ ያሰኘው አብ የገለጠለትና እርሱ የመሰከረው «አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ» የሚለው ምስክርነት እንጂ ራሱ ጴጥሮስ ለማንም መሠረት ሊሆን አይችልም፡፡ አጵሎስም ምንም ያህል በመጻሕፍት እውቀት የበረታና የጌታን መንገድ የተማረ ቢሆንም /ሐ.ሥ.18፡25/ መጻሕፍት የሚመሰክሩለት ጌታ ኢየሱስ እንጂ /ዮሐ.5፡39/ አጵሎስ ለማንም መሠረት ሊሆን አይበቃም፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ችግራቸውን ለመቅረፍ ሐዋርያው ለቆሮንቶስ አማኞች የሚከተለውን ጻፈላቸው፤ «አጵሎስ እንግዲህ ምንድነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው ያገለግላሉ፡፡ እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም፡፡ .. .. የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና» /1ቆሮ.3፡5-9/፡፡
እዚህ ላይ አማኞች የእግዚአብሔር ሕንጻ ከተባሉ የአንድ ሕንጻ ውበትና ጥራት የሚመዘነው ደግሞ በመሠረቱ ጥንካሬ ነውና ሐዋርያው በመቀጠል «የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናፂ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፤ ሌላውም በላዩ ያንጻል፤.. .. ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፤ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው» አላቸው /1ቆሮ.3፡11/፡፡ እንግዲህ አንድ ሕንጻ የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ ሊቋቋም የሚችለው በአለት ላይ ሲመሠረት መሆኑ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ እግዚአብሔርም እንዲሁ ሕንጻውን የሚመሠርተው በአለት ላይ ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔር አለት ደግሞ ማነው? ብሎ መጠየቁ አግባብነት አለው፤ ለዚህም ቅዱሳት መጻሕፍት መልስ አላቸው፡፡ ጌታ ሥጋ ለብሶ ወደዚህች ዓለም ከመግባቱ በፊት የተነገረው የትንቢት ቃልም እንዲህ ይላል፤ «እነሆ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን የከበረውን መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ የሚያምንም አያፍርም» /ኢሳ.28፡16/፡፡ ከዚህ ምንባብም እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ለቤቱ የሚሆንለትን መሠረት ራሱ ለማስቀመጥ እንደወሰነና ያም መሠረት 1ኛ/ የተፈተነ፣ 2ኛ/ የከበረ እና 3ኛ/ የጸና የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ በእርሱ የሚያምን ፈጽሞ እንደማያፍር መናገሩን እንረዳለን፡፡ ይህም መሠረት ሌላ ሳይሆን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን መሠረት ያስቀመጠው ራሱ እግዚአብሔር ከሆነ ሰው ሌላ መሠረት ሊመሠርት ቢሞክር ለእርሱ ባልተሰጠው ነገር መግባቱ ነውና ተጠያቂ ያደርገዋል፤ በተጨማሪም ሰው የሚመሠርተው መሠረት የተፈተነ፣ የከበረ፣ የጸናና የማያሳፍር ሊሆን እንደማይችል የሰው ልጅ የዘመናት ታሪክ በራሱ በቂ ምስክር ነውና በዚያ ሰው ሠራሽ መሠረት ላይ የተመሠረቱ ሁሉ የኋላ የኋላ የሚያፍሩ ይሆናሉ፤ «አወዳደቃቸውም ታላቅ» ይሆናል /ማቴ.7፡26-27/፡፡ የቆሮንቶስን አማኞች ለዚህ ችግር የዳረጋቸው ዋናው ምክንያት በማደግ ፈንታ በእግዚአብሔር እውቀት ህጻናትና የሥጋ ሰዎች እየሆኑ መሄዳቸው እንደነበር ሐዋርያው ሲገልጥላቸው «እኔም ወንድሞች ሆይ የሥጋ እንደመሆናችሁ በክርስቶስም ሕፃናት እንደመሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደመሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም ... ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ ሁለተኛውም እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?» /1ቆሮ.3፡1-4/ በማለት መከፋፈል በመካከላቸው በሆነ ጊዜ የነበሩበትን የመንፈሳዊ ሕይወት ብልሽት ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በመካከላቸው የተፈጠረው መለያየት በእግዚአብሔር ቃል አለማደግ ከመሆኑም ባሻገር አልፎ አልፎ በመካከላቸው የሚነሱ ውዝግቦችን የሚፈቱበትን መንፈሳዊ ጥበብን ማጣት እንደነበር የዚሁ መልእክት ሁለተኛ ምዕራፍ በይበልጥ ያስረዳል፡፡ የቆሮንቶስ አማኞች በሥነ ምግባር ችግር /ምዕ.5/፣ በግል ጠብ /ምዕ.6/፣ በጋብቻ ጉዳይና /ምዕ.7/፣ ለጣዖት የታረደ ሥጋን ስለአለመብላት /ምዕ.8-11/፣ ስለ ራስ መከናነብና አለመከናነብ /ምዕ.11፡1-16/፣ ስለ ጌታ እራት /ምዕ.11፡17-34/፣ ስለ ጸጋ ስጦታና ስለአምልኮ /ምዕ.12-14/፣ ስለትንሣኤ /ምዕ.15/.. ወዘተ በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ብዙ ችግ ነበረባቸው፡፡ እነዚህን ችሮቻቸውን በመንፈሳዊ መንገድ በመፍታት ፈንታ በአገልጋዮቻቸው ስም ቡድን አበጀተው ወደመለያየት አመሩ፡፡ ይህም ምን ያህል መንፈሳዊነት በመካከላቸው ተዳክሞ እንደነበር ያሳያል፡፡ ሰው በሥጋዊነት ተጽዕኖ ሥር ሲወድቅ የሚገጥሙትን አከራካሪ ጉዳዮችን በፍቅር እየዳኘ አንድነቱን በክርስቶስ ላይ በማጽናት ምትክ በግትርነትና በአልሸነፍም ባይ ስሜት እየተገፋ ያከራከሩትን ችግሮች ምክንያት አድርጎ ወደመለያየት ያመራል፤ ክርስቶስንም ትቶ በክርስቶስ አገልጋዮች ላይ ወደመመሥረት ይሄዳል፡፡ በቤተክርስቲያን ታሪክም የተፈጸመውና እስከዛሬም በክርስቶስ አካል ላይ ጠላት ሰይጣን እየፈጸመው ያለው ጥቃትም ከዚሁ የመነጨ እንደሆነ ግልጥ ነው፤ ይህ ደግሞ የሥጋዊነት መገለጫ ነው፡፡
በዘመናችን ያለው የክርስትና ዓለምም «መለኮታዊ ጠብዓያትን» በማጣት፣ «ሰው ብቻ» በሆኑ ሥጋውያን አማካኝነት፣ ከተመሠረተው አንድ መሠረት ውጭ በተለያየ ጊዜ በተነሡ አገልጋዮች ላይ ለመመሥረቱ ዋንኛው ምክንያት ቤተክርስቲያን ልትመራባቸው ለሚገቡ ለእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ትክክለኛ ስፍራ አለመስጠቱና በአማኞች መካከል የሚነሡ የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነቶች የሚፈቱበትን ጥበብ ማጣቱ እንደሆነ የሚጠራጠር ማን ነው? የቆሮንቶስ «ሥጋውያን አማኞች» ክርስቶስን ትተው በአገልጋዮች ስም የእምነት ጎራ ለይተው ለማምለክ በጣሩበት መንገድ ዛሬም ብዙዎች እየተጓዙበት መታየቱ የክርስትናው ዓለም አሳዛኝ ገጽታ ነው፤ በየምክንያቱ በሚፈጠር መለያየት የሚሰበሰቡ ሰዎች ግንባር ቀደም ሆነው በመሯቸው መሪዎች የግል አመለካከቶች ዙሪያ ወይም በወቅቱ ጎልቶ በታያቸው አንዳች እውነት ላይ ተመሥርተው ለተለዩት የእምነት ድርጅት ተፎካካሪ የሚሆን አንጻራዊ ድርጅት በምድር ላይ መገንባት ሲጥሩ ይታያል፡፡ የሚመሠርቱትንም ማህበር ደግሞ እንደ ቆሮንቶስ ሰዎች የጴጥሮስ ወይም የአጵሎስ ወይም ... ባይሉትም ልባቸውን የሞላ ወይም ልባቸውን ደስ ያሰኘ መንፈሳዊ እውነትን የሚገልጥ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲያገኙ በዚያ ቃል «እገሌ ቤተክርስቲያን» ብለው ይሰይሙታል፤ ለምሳሌ ምንም ያህል በእጅጉ ክቡርና የሚናፈቅ ቢሆንም ስለጌታ ምጽአት የሚናገረው እውነት በአንድ ወቅት ለእኛ ጎልቶ ስለታየን ብቻውን ክርስቶስን ተክቶ የማህበር መሠረት ሊሆንና «የምጽአት ቤተክርስቲያን» የሚሰኝ ቤተክርስቲያን እንድንመሠርት አያስችለንም፤ እንደማንኛውም የወንጌል እውነቶች ሁሉ የቅድስናም ሆነ የጥምቀት እውነት ወይም የመንፈስ ቅዱስና የጸጋ ስጦታ እውነት ወይም የብርሃን እውነት ወይም የትንሣኤ እውነት በራሱ የተወደደ ቢሆንም ክርስቶስን ተክቶ የቤተክርስቲያን መሠረት ሊሆን አይችልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በመለያየት፣ በጥላቻና በሰው ሠራሽ ሐሳብ ላይ የመሠረቱትን ማህበርም «የክርስቶስ ቤተክርስቲያን» የሚል ስያሜ ቢሰጡትም የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሊሆን እንደማይችል ሊታወቅ ይገባል፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከክርስቶስ ሞት የተገኘች እንጂ በሰው ስያሜ የምትመጣ መለያየትም የሚወልዳት አይደለችምና፡፡
ቤተክርስቲያን ክርስቶስ ባቀረበው መሥዋዕትነት መሠረት በበዓለ ሃምሳ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ተመሥርታለች፤ ዛሬ ሌሎች ስላስቀየሙን ወይም አስቀድሞ በሚገባ ያልተብራራ አንድ እውነት ለእኛ ስለተብራራልን ወይም በአንድ ስፍራ ቀድሞ ያላመኑ ሰዎች አግኝተን ልንመሰክርላቸው ስለቻልንና ስላሰባሰብናቸው ቤተክርስቲያን አትመሠረትም፤ ያላመኑ አዳዲስ ሰዎች በክርስቶስ ሲያምኑም ሆነ ባለማወቅ በተሳሳተና ሰው ሠራሽ በሆነ የክርስትና ሃይማኖት ውስጥ የነበሩት ሰዎች በነበሩበት ክፋት ላይ ነቅተውበት ራሳቸውን ከዚያ ዓመፃ ሲለዩ በትክክል እንዲሆን እግዚአብሔር የሚፈልገው ቀድሞ ወደ ተመሠረተችውና የክርስቶስ አካል ወደሆነችው አንዲት ቤተክርስቲያን ብልት ሆነው እንዲጨመሩና ክርስቶስ ራስ እንዲሆናቸው ነው እንጂ በአንዳች ስም አዲስ ወይም ሌላ ቤተክርስቲያን እንዲመሠርቱ ወይም ቀድሞ ለተመሠረተ የሃይማኖት ድርጅት ቅርንጫፍ እንዲሆኑ አይደለም፡፡
ነቢያትና ሐዋርያት በትምህርታቸው በመሠረቱት መሠረት ላይ አዳዲስና ከዓመፃ የሸሹ አማኞች ሕያዋን ድንጋዮች እየሆኑ እየተጨመሩ ያው የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ የተጀመረው ሕንጻ በማዕዘኑ በኢየሱስ ክርስቶስ እየተጋጠመ ያድጋል እንጂ አዲስ መሠረት ያለው አዲስ ሕንጻ አይሠራም /ኤፌ.2፡20-22፣ 1ጴጥ.2፡5/፡፡ ከዚህም አኳያ ሲታይ አሁን በሰው ልጆች በምድር ላይ እየተሠራ ያለው እንደ እግዚአብሔር ቃልና እንደ ጌታ ልብ አለመሆኑ የቅንጣት ያህል አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም አዲስ ሕንጻ የሚሠሩ ሁሉ አዲስ መሠረት ይጥላሉና፡፡ እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴም ምንጩ ሥጋዊነት ከመሆኑም ባሻገር ጉዳቱም ከልክ ያለፈ ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ሰዎች የሚጥሉት መሠረት ራሱ ክርስቶስ ስላልሆነ በዚያ ላይ የሚሰባሰቡት ሰዎች የተመሠረቱት በሕያው አለት ላይ አይደለምና በመካከላቸው የሚነሣው ጥቂቱ ክርክር ለታላቅ መለያየት ስለሚያበቃቸው እንደገና ለሌላ መከፋፈል ይዳረጋሉ፡፡ አሁንም ከተከፈሉ በኋላ በንስሐ ወደ እውነተኛው መሠረት በመመለስ ፈንታ በያዟቸው አቋሞች ላይ ስለሚመሠረቱ በድጋሚ እነርሱም ለሌላ መከፋፈል ይጋለጣሉ፤ እንግዲህ አሁን በምድር ላይ በክርስትና ስም የሚጠራው ሃይማኖተኛው ዓለም የዚሁ የሥጋዊነትና የእውነተኛውን መሠረት የመሳት ውጤት ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ይህ ክርስቲያኖች ነን በሚሉ ሰዎች መካከል የሚካሄደው መለያየት ከሚሰብኩት የፍቅር አምላክ ባሕርይ ጋር ስለማይጣጣም ስለ ክርስትና የሚሰጠው ምስክርነት ይደክማል፤ ስለሆነም እነዚህ ሰዎች በየጊዜው የሚፈጠረውን ክርክራቸውን በጌታ ፍቅር እየፈቱ ወደ ጌታ በመመለስ ፈንታ አገልጋዮቻቸውን እየተከተሉ ለሥጋዊ ምክንያት በማያባራ መለያየት ውስጥ ተዘፍቀው የተከፈሉት ሲከፈሉ እነዚያም ሲከፈሉ እንዲህም እያሉ በመከፋፈል «ምድርን እየሞሉ» ስናይ የክርስቶስ ልብ ምን ያህል እንደሚያዝንና ስለእርሱ የሚሰጠውም ምስክርነት ምን ያህል እየጎደፈ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ይህ ድርጊታቸው በጌታ ፊት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፤ «የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ» ከሚለው መለኮታዊ መመሪያ ውጪ በልዩ ልዩ ምድራዊና ሥጋዊ ምክንያቶች ቡድናዊነትን እየፈጠሩ የክርስቶስን መንጋ ከፋፍለው በራሳቸው መሠረት ላይ እንደ አዲስ የሚያንጹ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ እያፈረሱ እንደሆነ ቢያውቁ ምንኛ ፈጥነው ንስሐ በገቡ! «ማንም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ቅዱስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ» /1ቆሮ.3፡17/ የሚለውንስ አላነበቡም ይሆንን?
ሰው ሁል ጊዜ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ወደጎን በመተው «ቤተክርስቲያን» ብሎ የሚጠራውን በራሱ ሐሳብ ከመገንባት አላረፈም፤ በአንድ በኩል በገዛ እጁ የገነባውን የድንጋይና የእንጨት ቤት «እገሌ ቤተክርስቲያን» እያለ ይጠራዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በራሱ ሐሳብ ላይ የመሠረተውንና «እገሌ» ብሎ የሚሰይመውን ድርጅት «እገሌ ቤተክርስቲያን» ብሎ ይጠራዋል፤ ሆኖም ግን አንባብያን እዚህ ላይ ሊያውቁት የሚገባው ቁም ነገር እነዚህ በዚህ መልኩ የሚፈጠሩ ሁሉ «ቤተክርስቲያን» ተብለው ቢጠሩም መሠረታቸውን የሳቱ መሆናቸውን ነው፡፡
ዛሬ ጠላት ሰይጣን ከማናቸውም ጊዜ ባላነሰ መልኩ ሥጋዊነትን ተጠቅሞ ልዩ ልዩ ቡድኖችን ከቊጥር በላይ እስኪሆኑ ድረስ ባበራከተበት ዘመን ላይ ብንገኝም ቤተክርስቲያን ግን አንዲት ናት፤ ዛሬም ከሁለት ሺህ ዓመታት በኋላ መሠረቷ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ መሪዋም ያረገውና በክብር ያለው በቅድስተ ቅዱሳን በትከሻውና በልቡ ጽላት ላይ የአባሎቿን ስም በጋራና በግል ተሸክሞ በአብ ፊት የሚታይ ታላቁ ሊቀካህን ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡ ከምድራዊ የክርስትና ሃይማኖት ቡድናዊነት አምልጠው ወደዚህች መንፈሳዊት ማኅበር የደረሱ፣ «የጌታ ኢየሱስን ቃል ሰምተው የሚያደርጉ» /ማቴ.7፡24/፣ የፍጡራንን ስሞችና ሰው ሠራሽ አስተሳቦችን ትተው መሰብሰቢያቸውን የጌታ ኢየሱስ ስም ያደረጉ /ማቴ.18፡20/፣ እንደ ሰው ልማድ የማይመላለሱ ነገር ግን «የክርስቶስ ልብ» ያላቸው /1ቆሮ.2፡16/ እነርሱ በሕያው አለት በክርስቶስ ላይ ተመሥርተዋልና የአንዲቱ የክርስቶስ አካል ብልቶች ስለሆኑም ደስ ይላቸዋል፤ የአካሉን አንድነት ለመጠበቅና ነፍሳትንም ወደዚያች ለመጨመር የሚተጉ ከጌታ ብድራት አላቸው፡፡
እውነት አርነት ያወጣችኋል
ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» አላቸው/ዮሐ.8፡31/፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነት አርነት ያወጣችኋል» እያለ የሚናገራቸው አይሁድ በኃጢአት ባርነት ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሆኖም እነርሱ «የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፡- አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?» በማለት በባርነት መኖራቸውን መቀበል አልፈለጉም ነበር፤ ጌታ ግን «እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው» አላቸው /ዮሐ.8፡30-38/፤ እነዚህ አይሁድ «ያመኑ አይሁድ» እንደነበሩ ተብለዋል /ቊ.30-31/፡፡ ይሁንና ከነበሩበት የኃጢአት ባርነት ገና አርነት ያልወጡ ስለነበሩ እውነተኛ አማኞች ነበሩ ለማለት አይቻልም/ቊ.34፣44/፡፡ ዛሬም እንዲሁ ነው፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚሰሙና አምነዋል የተባሉ ነገር ግን ገና በብዙ የጥፋት ባርነት ሥር የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሳሉ «አርነት ወጥተናል» የሚሉና ለሌላውም አርነትን የሚሰብኩ ናቸው /2ጴጥ.2፡19/፤ እንደ እነዚህ ዓይነት ሰዎች «እውነት አርነት ያወጣችኋል» የሚለውን የኢየሱስን ትምህርት በእልከኛ ልብ ሳይቃወሙ ወደማስተዋል ተመልሰው ቢሰሙት መልካም ይሆንላቸዋል፡፡
የተለያየ የባርነት ቀንበር ተጭኖአቸው እየተጨነቁ የሚገኙና በአእምሮአቸው ሰላም አጥተው የሚኖሩ ሰዎች የሚመኙት ዋነኛ ነገር ቢኖር ቀንበሩን ሰብሮ ከተያዙበት ባርነት አርነት የሚያወጣቸውን ነገር ነው፡፡ «ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነው» ተብሎ እንደተጻፈው/2ጴጥ.2፡19/ ብዙ ወገኖች ከሥጋ ድካም የተነሣ ተሸንፈው ለማይፈልጉትና ለሚጐዳቸው ዓለማዊ ነገር በባርነት ሲገዙ ይታያል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የተያዙበትን የኃጢአት ባርነት የማያስተውሉና በአፍኣዊ እምነት የሚኖሩ ወገኖችም ይኖራሉ፤ እነዚህ ደግሞ «የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?» ብለው የመለሱለትን አይሁድ ይመስላሉ፡፡ ለእነርሱ እጅግ ጠቃሚ የሆነውን የአርነት ዜና ሲሰሙ «የአብርሃም ዘር ነን» በሚል ትምክህት ተይዘው ይህን ተቃራኒ መልስ መስጠታቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የኃጢአት ባሪያ መሆናቸውን አምነው አርነትን ቢፈለጉ ኖሮ ከተያዙበት ባርነት አርነት የሚያወጣቸውን እውነት ሊያውቁ በቻሉ ነበር፡፡ ብዙዎች አርነት ወደሚያወጣው እውነት ዘወር እንዳይሉ ዋነኛ ምክንያቱ ያሉበትን የባርነት ኑሮ አለማስተዋልና፣ በባርነት እንዳሉ ማመንን እንደውርደት መቊጠራቸው ነው፡፡ ነገር ግን በባርነት እየገዛቸው ባለው ነገር ላይ ባንነው አርነት መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ዛሬም ቢሆን ያለው የጌታ ትምህርት እውነት አርነት ያወጣችኋል የሚል ነው፡፡
ነገር ግን ሰው አርነት የሚያወጣውን እውነት እንዴት ያውቃል? ጌታችን ስለዚህ ሲናገር «እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ እውነትንም ታውቃላችሁ» ብሏል /ዮሐ.8፡31/፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት፣ በመማርና፣ በማንበብ ደረጃ ብዙዎች እውነትን ተረድተው ይሆናል፤ ጌታችን ግን «እውነትን ታውቃላችሁ» የሚላቸው በቃሉ የሚኖሩትን ነው፡፡ በዘመናችን በተለያዩ የሰው ዘዴዎች እየተነደፉ በመንፈሳዊ አገልግሎት ስም በእግዚአብሔር ሳይሆን በሰው የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ግን አማኞችን በተረዱት የእግዚአብሔር እውነት እንዳይኖሩ የሚያደርጉና ግራ የሚያጋቡ ናቸው፤ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎችም አማኞች በዚህ ዘመን ባለው የተሳሳተ ሥርዓተ አምልኮ ሳይጠመዱ ነጻ ሆነው በእውነተኛ መንገድ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ የማያበረታቱ እና ሰዎች በማያምኑበት የሐሰት ትምህርት ተጽዕኖ ሥር እንዲወድቁ የሚያደርጉ የባርነት አገልግሎቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ባለማወቅም ይሁን በስህተት በእንዲህ ዓይነት ባርነት የተያዙ ሰዎች በሚረዱት የእውነት ቃል ሊኖሩበት ይገባል እንላለን፡፡ እውነትን አውቀናል ማለት የሚችሉትም ያን ጊዜ ነው፡፡ እንዲህ ካደረጉም «በማላምንበት አምልኮና አስተምህሮ በተያዘ ሥርዓት ውስጥ ለምን እኖራለሁ? ሌሎችን አርነት የሚያወጣው ‹እውነት› ነው እንጂ የእኔ ጥበብ ነው እንዴ?» እያሉ በሐሳባቸው ሲያሰላስሉት ለነበረው ጥያቄ የሚያሳርፍ መልስን ያገኛሉ፤ እውነት ወደሚያጎናጽፋቸው እውነተኛ አርነትም ይወጣሉ !!
- ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና /2ቆሮ.13፡8/
- በእውነት ላይ አትዋሹ /ያዕ.3፡14//
- እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል /ኤፌ.4፡21//